ለሚሲዮናዊያን እንጸልይ
ማቴዎሰ 10፡ 5- 10
5እነዚህን አሥራ ሁለቱን ኢየሱስ ላካቸው፥ አዘዛቸውም፥ እንዲህም አለ። በአሕዛብ መንገድ አትሂዱ፥ ወደ ሳምራውያንም ከተማ አትግቡ፤ 6 ይልቅስ የእስራኤል ቤት ወደሚሆኑ ወደ ጠፉት በጎች ሂዱ እንጂ።
7 ሄዳችሁም። መንግሥተ ሰማያት ቀርባለች ብላችሁ ስበኩ። 8 ድውዮችን ፈውሱ፤ ሙታንን አስነሡ፤ ለምጻሞችን አንጹ፤ አጋንንትን አውጡ፤ በከንቱ ተቀበላችሁ፥ በከንቱ ስጡ። 9 ወርቅ ወይም ብር ወይም ናስ በመቀነታችሁ፥ 10 ወይም ለመንገድ ከረጢት ወይም ሁለት እጀ ጠባብ ወይም ጫማ ወይም በትር አታግኙ፤ ለሠራተኛ ምግቡ ይገባዋልና።
የሰማይ አባታችን ሆይ በምድራችን እና በዓም ዙሪያ ስላሉ ሚሲዮናዊያን እናመሰግንሃለን፡፡ እግሮቻቸው የምስራቹን ይዘው ስለተጓዙ ፤ ስላላቸው መሰጠት እና ትጋት እናመሰግንሃለን፡፡ ስምህ በምድር ሁሉ ላይ ይታወቅ ዘንድ ምስክሮች ስለሆኑህ እናመሰግንሃለን፡፡
መንፈስ ቅዱስ በምድር ዙሪያ ያሉ ሚሲዮናዊያን ልጆችህን በመንፈስህ ሃይል እና በፈቃድህ እውቀት ሙላቸው፡፡ ይበልጥ ልባቸው ለአንተ ባለ ፍቅር እንዲሞላ እንለምንሃለን፡፡ በሁለንተናዊ መንገድ ባርካቸው፤ ቤታቸውን እና ቤተሰቦቻቸውን እንድትጠብቅ፣ በሚያስፈልጋቸው ሁሉ አብረሃቸው እንድትቆይ እንለምንሃለን፡፡
ስምህ ባልተጠራበት ቦታ ስለስምህ ዋጋ ሊከፍሉ ቆርጠዋና ቅደምላቸው፡፡ መንፈስህ እያበረታ ያስቀጥላቸው፡፡
ይህን በምትወደው ልጅህ ለመነህ! አሜን!